በጎፋ ዞን ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶችና ሕፃናት የእርባታ ዶሮዎችን ድጋፍ አደረገ።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥምረት ከክልሉ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር በጎፋ ዞን ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶችና ሕፃናት የእርባታ ዶሮዎችን ድጋፍ አደረገ።

ሣውላ፣ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥምረት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ፣ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በድንገተኛ የመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶችና ሕፃናትን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል የእርባታ ዶሮዎችን ድጋፍ አድርጓል።

በዛሬው ዕለት በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ለ60 እማወራዎች ለእያንዳንዳቸው 15 የእርባታ ዶሮዎችን ጨምሮ ለሴቶችና ሕፃናት የሚሆን የአልባሳት ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥምረት መስራችና ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ኢትዮጵያ አለማየሁ ድጋፉ በ19 ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ባዋጡት ገንዘብ የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች የሚችሉትን ድጋፍ በማድረግ ላሳዩት ኢትዮጵያዊ ወገናዊነት በራሳቸውና በፕሮጀክቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ (ኢንጂነር) የፕሮጀክቱ ፕሬዚዳንት ጨምሮ የቦርድ አመራሮች በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ላደረጉት ድጋፍና ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጎጂ ቤተሰቦች ስም አመስግነዋል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶችና ሕፃናት ወላጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በሞት ያጡ መሆናቸውን ገልጸው፣ ተጎጂዎችን በቋሚነት ሕይወታቸውን ለመቀየርና ለማቋቋም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የዞኑ መንግስት ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳትና በዶሮ እርባታ፣ በወተት ላም፣ በበግና ፍየል ማሞከት ፕሮጀክቶችን ያዘጋጀ መሆኑን ኢንጂነር ዳግማዊ ጠቁመው፣ ኢትዮጵያውያን በእነዚህ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ካሰች ኤልያስ በበኩላቸው ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥምረት በ19 ሀገራት ውስጥ የሚሰራና በበጎ ፈቃደኞች የተመሠረተና ለትርፍ ያልተቋቋመ የበጎ አድራጎት ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፣ ፕሮጀክቱ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችና ሕፃናትን ደርሶ የመደገፍ ዓላማ የያዘ ነው ብለዋል።

ወ/ሮ ካሰች አክለውም አደጋው ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ቢሮው ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለተጎጂዎች ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፣ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች አደጋው በተከሰተበት ስፍራ ተገኝተው ለተጎጂዎች ላደረጉት ድጋፍ በራሳቸውና በቢሮው ስም ምስጋና አቅርበዋል።